በምስራቅ ጎጃም ዞን የግብርና ምርምር ተቋም ለመገንባት የመሰረት ድንገይ ተቀመጠ፣ የምርምሩ ስራ ከዚህ አመት ጀምሮ ከግንባታው ጎን-ለጎን ይካሄዳል ተባለ፡፡

በምስራቅ ጎጃም ዞን የግብርና ምርምር ተቋም ለመገንባት የመሰረት ድንገይ ተቀመጠ፣ የምርምሩ ስራ ከዚህ አመት ጀምሮ ከግንባታው ጎን-ለጎን ይካሄዳል ተባለ፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን በአለም አቀፍ የልህቀት ማዕከል ደረጃ የሚያስገነባው ‹‹የደብረ ማርቆስ የግብርና ምርምር ማዕከል›› የግንባታ መሰረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ ስርዓት የካቲት 23 ቀን 2011 ዓ.ም በአነደድ ወረዳ በዮቢ እንቻፎ ቀበሌ ከፍተኛ የፌደራል እና የክልል የዞን አመራሮች በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ ተካሂዷል፡፡

የደብረ ማርቆስ የግብርና ምርምር ማዕከል ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ ስርዓት ላይ ከፌደራሉ እርሻ ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ተወካይ ክብርት ወይዘሮ አይናለም ንጉሴ፤የፌደራል ግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ማናደፍሮ ንጉሴ፣ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ቦሰና ተገኘ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ አየነው በላይ በጋራ ሁነው የማዕከሉ ግንባታ መጀመሩን የሚያበስረውን የመሰረተ ድንጋይ መጋረጃ በጋራ ገልጠዋል፡፡ በመሰረት ድንጋዩ ላይ በእብነበረድ ላይ የተቀረጸው ጽሁፍ የማዕከሉ የመሰረት ድንጋይ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው መቀመጡን የሚገልጽ ሲሆን ተወካያቸው አቶ አይተነው ክቡር ርዕሰ መስተዳደሩ በስነ ስርዓቱ ላይ ለመገኘት ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበራቸውና በኘሮግራማቸውም የተያዘ የነበረ ቢሆንም ከአንድ ቀን በፊት በአስቸኳይ አገራዊ ጉዳይ መገኘት አለመቻላቸው ገልጸዋል፡፡

በዚሁ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙ ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጀምሮ በተለያዩ የመንግስት የአስተዳደር እርከን የሚገኙ የተለያዩ ተቋማት አመራሮችና ባለሙያዎች በምስራቅ ጎጃም ዞን የግብርና ምርምር ተቋም ማቋቋም ፋይዳውና ይህንኑ ዕውን ለማድረግ ያለፉባቸውን ውጣ ውረዶች እና ያንንም ሁሉ አልፈው ሕልማቸው እውን ለመሆን በመብቃቱ የተሰማቸውን ደስታ ጭምር በየተራ አሰምተዋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ግብርና ምርምር ተቋም የግንባታ የመሰረት ድንጋይ በተቀመጠበት በዮቢ እንችፎ ቀበሌ ለተገኙ እንግዶች የ‹‹እንኳን ደህና መጣችሁ!›› እና ‹‹ለ123ኛው አመት የአድዋ ድል በዓል እንኳን አደረሳችሁ!›› በማለት የንግግር መድረኩን የያዙት የአነደድ ወረዳ አስተዳዳሪ አተ አሳዬ በቀዳሚነት ለምርምር ማዕከሉ የተከለለውን አርባ ሶስት ሄክታር መሬታቸውን ለለቀቁት 50 ያህል የዮቢ አናቸፎ ቀበሌ አርሶ አደሮች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በምስራቅ ጎጃም ዞን የግብርና ምርምር ተቋም ጥያቄ ረዥም ዘመናት ያስቆጠረ መሆኑን ያስታወሱት አቶ አሳዬ ጥያቄውን ሲያቀርቡ ለነበሩ የዞኑ ባለሙያዎችና አመራሮች እንዲሁም ለፌደራሉና ለክልሉ የግብርና ምርምር ተቋማት ኃላፊና ባለሙያ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የምስራቅ ጎጃም ዞን አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አለኸኝ የምስራቅ ጎጃም አርሶ አደር ጠንካራና ታታሪነት ዞኑን በምርታማነቱ ታዋቂ አድርጎታል ካሉ በኋላ በዞኑ የሚካሄደው የግብርና ስራ በምርምር ቢታገዝ ደግሞ ምርትና ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ የአርሶ አደሩን ገቢ፣ የክልሉንም ሆነ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት በማመን ጥያቄው ለሚመለከታቸው አካላት ከቀረበ ረዥም አመት መቆጠሩን አቶ አብርሃም አስታውሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ ጥያቄው ምላሽ ሳያገኝ አመታት በመቆጠሩ ተስፋ ወደ መቁረጥ ደረጃ በደረሱበት ጊዜ ከተጠየቀውና ከታሰበውም በተለየ የአለም አቀፍ የልህቀት ማዕከልነትን ራዕይ የያዘ በፌደራሉ ምርምር ተቋም የሚመራና የሚተዳደር ማዕከል እንዲገነባ ውሳኔ ላሰተላለፉት የፌደራል የግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት አመራሮች ምስጋናቸውን
አቅርበዋል፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ቦሰና ተገኘ በኢትዮጵያ ከሚመረተው ሰላሳ አምስት መቶኛ ሰብል በአማራ ክልል ድርሻ መሆኑን አስታውሰው ምስራቅ ጎጃም ዞን ደግሞ ከአማራ ክልል ሰፊ ድርሻ ያበረክታል ብለዋል፡፡ የምስራቅ ጎጃም ዞን ተፈጥሯዊ ጸጋ ለሰብል ምርት ምቹና ተስማሚ ነው፡፡ እስካሁን በዚህ ዞን ከፍተኛ ምርት ማምረት የተቻለው ትጉህና ታታሪው አርሶ አደር በተወሰነ ደረጃ ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉ ቴክኖሎጅዎች በመጠቀሙ ነው፡፡ በዕለቱ የመሰረተ ድንጋይ የተቀመጠለት የግብርና ምርምርም ተቋም የዞኑን የምርታማነት ማነቆዎችን በመለየት ለአካባቢው ተስማሚ ቴክኖሎጅዎችን ማፍለቅ ያስችላል ብለዋል የቢሮ ሓላፊዋ፡፡ #የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ ግብ አይደለም; ያሉት ዶ/ር ቦሰና የተቁሙ ወደ ስራ መግባት ቢሮው ተልዕኮውን ለመወጣት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት በመሆኑ ግንባታው በተያዘለት ዕቅድ መሰረት ተጠናቆ ወደ ስራ መግባት ይኖርበታል፣ ቢሮውም የሚጠበቅበትን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

‹‹የደብረማርቆስ የግብርና ምርምር ማዕከል ወደስራ ለመግባት የግንባታውን መጠናቀቅ አይጠብቅም፤ ተቋሙ የምርምር ስራውን ከዚህ አመት ጀምሮ ወደስራ ይገባል፤›› በሚለው መልዕክታቸው በታዳሚው ደስታ ላይ ደስታ የሚያጭር መልክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢኒስቲትዮት ዳይሬክተር ዶ/ር ማናደፍሮ ንጉሴ ናቸው፡፡
( የዶ/ር ንጉሴንና በሌሎች አካሎች ግንባታውን በተመለከተ የተሰነዘሩ እስተያየቶች በቀጣይ የሚቀርቡ ይሆናል፡፡) አዘጋጁ

publicrelation